በግጥም እንነጋገር

Wednesday, April 18, 2012

የምን ያህሉሽ ሻይ ቤት


           ቀትር  ላይ  አባይ  ፏፏቴ  አካባቢ  ሙቀቱ  ልብ  ያቆማል !፡፡ ሙቀቱ  ግን  ያቃጥልም……. የሆነ ደስታ  የሚፈጥር  ስሜ ግን አለው ፡፡ ፏፏቴውን ለመጎብኘት አብረን ከተጓዝን ጓደኞቼ አንዱ በጣም ደክሞታል ፡፡  ጠምቶታልም፤ እናም በአካባቢው የሚኖሩ ትንንሽ  ልጆች  አስጎብኚዎቻችን  አረፍ  ልንል የምንችልበትና  ሻይ  ቡና ለማለት የምንችልበት ቦታ እንዳለ  በመጠቆም በነሱ መሪነት ሽቅብ ወደ ተራራው ወጣን፡፡
        አሁን  የአባይ  ፏፏቴ  አናት  ላይ  ጉብ  ብለናል ፡፡ ቁልቁል  የሚወረወረው  ጢስ  አባይ  ፏፏቴ  ልብ ይመስጣል ፡፡  ለእይታ  ምቹ  በሆነ  ቦታ ላይ አንድ  ግንድ ተደግፋ  በሳጠራ  የተከለለች  የወ/ ምን ያህሉሽ  ብቸኛ   ሻይ  ቤት  ትታያለች ፡፡   ማመን አቃተኝ…..የመግቢያ  በሯ  ጠባብ  ነው ፡፡    ተራ በተራ ወደ  ውስጥ  መዘለቅ  የግድ  ነው ፡፡ ሁለት  ጥንድ  ጓደኛሞች   የመስሉኝ   ተስተናጋጆች  ብቻ   ተቀምጠዋል ፡፡  እኛ  ስንጨመር  ቤቷ ሞላች ፡፡ / ምንትዋብ  እንግዶቿን  ለማስተናገድ  ተፍ ተፍ እያሉ ነው፡፡  ሞቅ ያለ ሀገራዊ  ሰላምታ  በመስጠት  ተቀበሉን …….ቤቷ ጠባብ ነች  በሁለት  ረድፍ መደዳውን ጨርቅ  የለበሱ  ድንጋይ  ተደርድረዋል ፡፡ ለመቀመጫነት ያገለግላሉ ግድግዳው  የሳጠራ ሆኖ  ውስጡን  ለማሳመር  በሀገሬ   ሸማኔዎች  የተጠበቡበት  የተለያየ  ባህልን  በሚያንፀባርቁ ጨርቆች  ተሸፍኗል ፡፡ እንዴት ያምራል መሰላችሁ…..! ፡፡ ፊት ለፊት  በሰፌድ  ላይ  የተቆራረጠ የአንባሻ  ዳቦ  በዳንቴል  ሹራብ  ተሸፍኖ  ተቀምጧል ፡፡ ሁለት ትልልቅ  ትኩስ  ሻይ  የተሞሉ ፔርሙዞች፣ አንድ  በለስላሳ  መጠጦች  የተሞላ   ሳጥን፣ እጅግ  በጣም  የሚያምር መልኩ  የተሰራ ረከቦት  በርካታ  የቡና  ሲኒዎችን  ደርድሮ  መሀል  ላይ  ጉብ  ብሏል !፡፡  የቡና  ጀበናው ትርክክ ብሎ  ከተቀጣጠለው  የከሰል  ምጣድ  ላይ  ተጥዶ  ሽቅብ  የሚተነፍሰው  እንፋሎት  የቡናውን  መድረስ እየጠቆመ ነው ፡፡  / ምን  ያህሉሽ  እድሜያቸው  ወደ  ሀምሳዎቹ  አጋማሽ  ላይ  የሚገመት አጠር ያሉ  ጠይም  መልከ  መልካም  የደስ  ደስ ላቸው  ናቸው ፡፡  እጣኑን ጨስ አድርገው  እንኳን ደህና መጣችሁ ምን ልታዘዝ .. አሉን፡፡  ሁሉም  የፍላጎቱን  አዘዘ   የኔ  ምርጫ   ቡና  ነው፤ ምናልባት አላውቅም   በአባይ  ውሃ የተፈላ  ቡና ሊሆን ይችላል .! እየጣፈጠኝ  ጠጣሁ  ደገምኩ ቡናዬን ፉት እያልኩ ውስጤ አንድ ጥያቄ  አጫረ……፣  በዚህ  የሚያምር  ታሪካዊ  ቦታ  እንዴት  አንድ  ደረጃውን  የጠበቀ  ሆቴል  ወይም  ሎጅ  አይኖርም  ?  ፡፡ የክልሉ  መንግስት  አያውቀውም  ቦታውን ? እንዴትስ  የእኛ  ባለሀብት  ይሄን  ሃላፊነት  የሚወስድ  ጠፋ ?  ፡፡ አንድ ግን  ከሳጠራዋ  ሻይ ቤት በስተቀኝ  መሰረቱ  ተጀምሮ  የአረም  ዳዋ  ለብሶ  በጅምሩ  የቀረ  እንቅስቃሴ  አይቻለሁ ፡፡  በውስጤ ሲመላለስ  የነበረውን  ጥያቄ  ለወ/  ምን ያህሉሽ  አቀረብኩ
 ይሄ እዚህ ጋር የሚታየው የህንፃ መሰረት ማነው የሰራው?” አልኳቸው
 ጊዜው  ቆይቷል አንድ ባለሀብት ነው መሰረቱን ጀምሮ በዛው ጠፋ ምክንያቱን ግን አላወኩም  ፡፡ታድያ  እንደው  የክልሉ  ባለስልጣናትስ  ወይም  ባለድርሻ  አካላት  ምንም  ሊያደርጉላችሁ  አልቻሉም ? "  ብዬ ሌላ ጥያቄ ጨመርኩ፡፡ /  ምን ያህሉሽ  በስራ  ተጠምደዋል  ብቻቸውን  ናቸው የሚያግዛቸው  የለም  ጥንካሬያውን  አደነኩኝ  ትንሽ  የእረፍት  ጊዜ  ሲያገኙ  ለጥያቄዬ  መልስ ለመስጠት ተዘጋጁ፡፡
"ምን ነበር ያልከኝ ? አዎ ምን ባክህ አንድ ጊዜ ስልጣናቸወን ባላውቅም ከመንግስት ተልከን ነው የመጣነውብለው  ገበያው እንዴት ነው ምናምን  ብለው  ጠይቀውን  በቃ  በቅርቡ  እዚህ  ጋር  ትልቅ  መዝናኛ  ይከፈታል  አሉና  ሄዱ  ይኸው  እስከ  ዛሬ  የውሃ  ሽታ  ሆነው  እንደቀሩ ነው ፡፡ ምንም ያየነው ነገር የለም  እኛ  ግን  እንደ  አቅማችን  ጎብኚውን   እያገለገልን  ትንሽም  ቢሆንም  እየተጠቀምን  እንገኛለን፡፡ አሉና  አንገታቸውን  አቀረቀሩ…..፡፡ ትንሽ  ቆዩናም  እንዲህ  ሲሉ  ጠየቁኝ፡፡
         ልጄ ምናልባት ታገኛቸው እንደሁ ንገራቸው…….. ንገራቸው  ምነው ጠፋችሁ በልልኝ  ፡፡ አሉና  አደራም  ጭምር  አሳቀፉኝ  ፡፡ ጨዋታቸው  ይጣፍጣል  ብዙ  ልንጫወት  በወደድኩ  አዳዲስ እንግዶች  እየገቡ   ነው ፡፡  ወደ ዛው  መሄድ  አለባቸው  ከዚህ  በላይ  መቆየት አይችሉም፡፡  "ምነው ጠፋችሁ በልልኝ…..! አይደል  ያሉኝ  ጊዜው  እንዴት  ይሮጣል  …..ቀን ሳምንትን  ሳምንት  ወራትን ወራት  አመታትን   ሊደፍን  ጥቂት ቀረው ፡፡  ይኸው  የወ/ ምን ያህሉሽን  ቁጭት  ጥያቄና  አደራ በልቤ  መዝገብ   ተፅፎ   እንደተከደነ   አብሮኝ   እንደተቀመጠ   ነው   ምኞታቸው  ተሳክቶ  ይሆን ? ፡፡
*         *        *
               ሻይ ቤቷ ሞቅ ደመቅ  ብላለች ጓደኞቼ በግልና በጋራ ጉዳዮች ተጠምደው እየተጨዋወቱ  ነው፡፡ ድንገት ዞር ስል ከሳጠራ ሻይ ቤቷ ውጪ ከአባይ ፏፏቴው ፊት ለፊት በግማሽ ከመሬት የተቀበረ ድንጋይ ላይ  የተቀመጠች  ወጣት ልጅ ላይ አይኔ ተተክሎ ቀረ፡፡  ከላይ እስከ ታች ጥቁር  በጥቁር  የሆነ ቀሚስ ለብሳለች ፀጉሯም በጥቁር ሻሽ ተሸፍኗል፡፡ አዎ አልተሳሳትኩም ቅድም ከአራት ሴት ጓደኞቿ ጋር ከፏፏቴው ስር አይቻታለሁ፡፡ አሁን ግን ብቻዋን ነች፡፡ ጀርባዋና ለሻይ ቤቷ ሰጥታ አንገቷን ከጉልበቷ ቀብራ ተቀምጣለች፡፡ ምን ሆና ነው? ምን ይሆን የምታስበው? ለምንስ ከጓደኞቿ ጋር ተነጥላ መቀመጥ ፈለገች? ምክንያቷን ለመስማት ጓጓሁ እናም ፈራ ተባ እያልኩ አጠገቧ እንደደረስኩ እግሮቼ ላይ ቁጢጥ ብዬ ተቀመጥኩ እንዴት ብዬ ልጀምር…… ጨነቀኝ፤ እንደምንም ወኔዬን አሰባሰብኩና እንዲህ አልኳት::……….. ይቀጥላል

2 comments:

  1. እግዚአብሔር ይባርክህ መስመርህ ለይ ነህ የሚጠፍጥ ግጥም ከነትረካው በአንተ በጣም ኮራሁ ወዳጅህ ዳዊት

    ReplyDelete
  2. Adem It is really wonderful and interesting script.

    ReplyDelete